ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ እናቶች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ

ጥር 1/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የእናቶች ሞት መጠንን በመቀነስ ረገድ ለውጦች እየተገኙ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡
እንደ ሀገር በወሊድ ወቅት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በተሰሩ በርካታ ስራዎች የሞት ቁጥሩን መቀነስ ቢቻልም አሁንም በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
የጤናማ እናትነት ወር ከጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የዘመቻ ንቅናቄዎች ይከበራል።
ሚኒስትሯ ዘመቻውን ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ “ከወሊድ በኋላ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንግታ” በሚል መሪ ቃል ዘመቻው እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ በተለይ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ የእናቶችን ህይወት ለመታደግ ጤና ሚኒስቴር ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የአንቡላንስ ግዢና ሌሎች የጤና ህክምና ተደራሽነት ላይ በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሸባሪው ሕወሓት በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመትና ዘረፋ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት የሚኖርን የእናቶች ሞት ቁጥር እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማቱ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲመለሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የጤናማ እናትነት ወር በዓለም ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ16ኛ ጊዜ በጥር ወር ይከበራልም ነው የተባለው፡፡
መስከረም ቸርነት