ከኦነግ ሸኔ ጋር ያበሩ ከ1000 በላይ ፖሊሶች እርምጃ ተወሰደባቸው፤ 1 ሺ100 በላይ የኦነግ ሸኔ አባላት ተደምስሰዋል

በፀጥታ እና ፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ሰዎችን አደራጅቶ በመያዝ ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚሰሩ አካላትን ጨምሮ ከ1000 በላይ የፖሊስ አባላት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት ከኦነግ ሸኔ ስልት ውስጥ የሽምቅ ኃይል አደረጃጀት፣ በመጠቀም በተለያየ ሁኔታ ህዝብ ውስጥ መደበቅ ፣መረጃ ለማግኘት ደግሞ መዋቅር ውስጥ በተለይም ደግሞ የፀጥታና የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ሰርጎ መግባትና ሰዎችን አደራጅቶ በመያዝ እኩይ  ተግባሩን ለመፈፀም የተለያዩ  ሙከራዎችን አድርጓል።

የቡድኑን ይህን መሰል አካሄድ በማጥናትና ሰፊ ግምገማ በማድረግ ከ1000 በላይ በሚሆኑ የፖሊስ አባላት ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ የማጽዳት ስራዎች መሰራታቸውን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፣ እርምጃው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በቡድኑ የጥፋት ተልእኮ አልፎ አልፎ የሚሳተፉ፣ የሚጠረጠሩ፣ መረጃ የሚሠጡ፣ ከእነርሱ ጋር የሚያብሩ፣ ከጎሰኝት፤ ከከባቢነትም ተነስተው ከፀጥታ መዋቅርና አመራር ጋር በሚመሳጠሩት ላይ በየወቅቱ ግምገማዎች እየተካሄደ እርምጃ እንደሚወሰድ ያስታወቁት ኮሚሽነሩ ፣ ኃላፊነት ኖሯቸው ኦነግ ሸኔን አምርረው በማይተጋሉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።