የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው

ሰኔ 2/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮች የምዝገባ ሂደት እና ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች ያገጠሟቸውን ችግሮችን እንዲገልፁ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በርካታ ፓርቲዎች  በመንግስት ጫና እየደረሰብን ነው ያሉ ሲሆን  በተለይም የምርጫ ጉዳይ የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች ለብልፅግና ፓርቲ በማድላት ለእኛ ጥያቄ ምላሽ እየተሰጡ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ለቦርድ አቅርበዋል::

አቶ ዛዲግ አበረሃ ከብልፅግና ፓርቲ ፓርቲዎቹ የሚያነሱት ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ያጣራልን ብለዋል

አቶ ዛዲግ አክለውም የቀረበው ቅሬታ እዉነት ከሆነ መንግስት እርምጃ እና ማሻሻያዎችን ይወስዳል ብለዋል።  ምርጫ ቦርድም በቀሩት ቀናት የተነሱ ችግሮችን ቦርዱ ባለው ስልጣን መሠረት ለመፍታት ይሠራል ተብሏል።

የሐረሪ ክልል ምርጫ ይካሄዳል ወይ ሲል ብልፅግና ፓርቲ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ያነሳ ሲሆን የሐረሪ ክልል ጉዳይ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ምርጫ አይካሄድም ሲሉ የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አስታውቀዋል ::

የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት የኢንተርኔን መቆረረጥ፣ በህትመት ወቅት ትክክለኛ መረጃ አለመሟላት ችግር እንደገጠመው ቦርድ አስታውቋል፡፡

በዚህም 60 የምርጫ ክልሎች ትክክለኛ መረጃ በመያዝ መታተም የነበረባቸው  ነገር ግን ትክክለኛ መረጃ ሳይዙ መውጣታቸውን ቦርድ አረጋግጫለው ብሏል።

ለተፈጠረው ስህተት  የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን በቦርድ የሚሰሩ እና ሀላፊነታቸውን ባልተወጡ ሠራተኞች ላይም እርምጃ መውሠዱን አስታውቋል ::

(በሜሮን መስፍን)