የውጭ ጣልቃ ገብነትን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲቃወም ጥሪ ቀረበ

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው የውጭ ጣልቃ ገብነትን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እንዲቃወም ታዋቂ ግለሰቦች ጥሪ አቅርበዋል።
ጉዳዩ ይመለከተኛል ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች “ብሔራዊ ክብር በሕብር” ሲሉ በሰጡት መግለጫ በሁሉም ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም የሀገሪቱን ህልውና መታደግ አለባቸው ተብሏል።
የውጭ ተጽእኖ የሚፈጥሩ አካላትም ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ ጥሪ አቅርበዋል።
“ኢትዮጵያውያን ድሃ ብንሆንም የሀገራችንን ክብር አሳልፈን አንሰጥም” ነው ያሉት በሰጡት መግለጫ።
ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የውጭ አካላት እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የተላለፈውን መልእክት እንዲቀላቀሉ ነው ታዋቂ ግለሰቦቹ ጥሪ ያቀረቡት።
“ለሀገራችን አምቢ አንበል” በሚል በቀረበው ጥሪ አሜሪካ እና አቻዎቿ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና መቃወም ይገባል፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ተገቢነት የጎደለውና ኢትዮጵያን አንደ ሀገር ያለመቁጠር በመሆኑም ይህን ለመቃወም የትኛውንም መንገድ አንጠቀማለን ብለዋል።
ውጫዊ ጫናዎች ሶስት መሠረታዊ ክንውኖችን መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት ታዋቂ ግለሰቦቹ እነዚህም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለተኛ ሙሊትን፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻንና የሕዝብ መብት የሆነውን ምርጫ አስታከው ጫና እያደረጉ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ብሔራዊ ክብር በሕብር” በሚል ሕዝቡን አስተባብሮ ጣልቃ ገብነት እጆችን እምቢ የሚል ንቅናቄ መፍጠር እንዳለበት ነው ተጠቁሟል።
(ምንጭ፡- አሚኮ )