ክልሉ የተረጋጋ በመሆኑ የህዝቡ ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

መጋቢት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካ ስነ – ምህዳር በመፈጠሩ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየተፈቱ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

“ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ክልላዊ ኮንፈረንስ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።

የፓርቲው የግማሽ የምርጫ ዘመን ግምገማ እና የወደ ፊት ችግሮች እንዴት ይቀረፋሉ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ መፍትሄ ለማስቀመጥ እና የነገ አቅጣጫን ለመቀየስ የተመረጡ 1ሺሕ ስምንት  የሚሆኑ አባላት በተገንኙበት ኮንፈረንሱ ተካሂዷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት ብልፅግና ፓርቲ በግማሽ የምርጫ ዘመኑ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በማለፍ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቡ ችሏል።

የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በሥራ እድል ፈጠራ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታቸው ላቅ ያለ ቢሆንም ዛሬም በርትተን ሰርተን የኑሮ ውድነትን መቀነስ የሚያስችል አቅም ሊኖረን ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ አልፎ አልፎ የሚታየውን የሰላምና ፀጥታ ችግር ለመፍታት በየአካባቢው ያሉ የፓርቲው አባላት፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል እና የፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይል በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡

አሁን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠል የወንድማማችነት እሳቤ እና መተሳሰብ በእጅጉ ያስፈልገናል ሲሉም ገልጸዋል።

ካሳነሽ ፋንታሁን (ከቦንጋ)