በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናዊያን በባለቤትነት የሚተሳተፉበት ሁሉን አቀፍና አካታች ውይይት ያስፈልጋል – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

መጋቢት 13/2016 (አዲስ ዋልታ) በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናዊያን በባለቤትነት የሚተሳተፉበት አፍሪካ መር፣ ሁሉን አቀፍ እና አካታች ውይይት ያስፈልጋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ሚኒስትሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት የተዋቀረውን የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ፓናል ቡድን አባላትን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በወቅቱ በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናዊያን በባለቤትነት የተሳተፉበት እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሁሉን አቀፍ እና አካታች ውይይት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚኒስትሩ በተለይም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር የሚከናወኑ የሰላም አማራጮችን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

በሱዳን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለተዋቀረው የሱዳን ፓናል ኢትዮጵያ ደስተኛ መሆኗን እና የምትችለውን ድጋፍ ሁሉ እንደምታደርግም ቃል ገብተዋል።

የተዋቀረው ቡድን ሊቀመንበር ሙሀመድ ኢብን ቻምባስ በበኩላቸው በግጭቱ ምክንያት ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስና ተያያዥ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ፓናል በህብረቱ (Silencing the Guns) ልዩ ልዑክ በሆኑት ሙሃመድ ቻምባስ የሚመራ ሲሆን የኡጋንዳ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰፔሊኦዛ ካዚኮዌ እንዲሁም የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት የሱማሊያ ልዩ ተወካይ አምባሳደር ፍራሲስኮ ማድራን በአባልነት ያቀፈ ነው ተብሏል።