ኮሚሽኑ ለመተከል ተፈናቃዮች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለመተከል ተፈናቃዮች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

በኮሚሽኑ የአሶሳ አስተባባሪ ቪክቶሪያ ኮፓ ድጋፉን ዛሬ በአሶሳ ከተማ ለክልሉ አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል፡፡

አስተባባሪዋ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ የመተከልን ተፈናቃዮች ለመደገፍ ከክልሉ  ጋር በመቀናጀት እየሠራ ነው፡፡

ከድጋፉ መካከል 13 ሺህ ብርድ ልብሶች እንዲሁም የአልጋ አጎበሮች፣ ምንጣፎች፣ የተለያዩ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል፡፡

ይህም ከአራት ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስተባባሪዋ አስረድተዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ በበኩላቸው፤ በመተከል ዞን የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን በመንግስት አቅም ብቻ ለመደገፍ አዳጋች በመሆኑ መንግሥት ኀብረተሰቡን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ረጂ ድርጅቶችም እንዲያግዙ ጥሪ መቅረቡን አስታውሰው፣ ጥሪውን ተቀብሎ ኮሚሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰጠው ምላሽ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ድጋፉ በዞኑ በርካታ ተፈናቃዮች በሚገኙበት ቡለን እና ድባጤ ወረዳዎች በአጭር  ቀናት ውስጥ እንደሚደርስ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡