ኮሚሽኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ

ሰኔ 20/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ፡፡

ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንዳለ ይታያል ብሏል፡፡

ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት መፍታትና ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጿል፡፡

እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ በሂደትም የመተማመንን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት እንዲቻል ገለልተኛ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ ተመላክቷል፡፡

ስለሆነም በውጭ ሀገራት የሚትኖሩ ኢትጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅመው በኢትዮጵያ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይህንንም ለማስፈፀምም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የበይነ መረብ (ዙም) ስብሰባ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በዚህ መሰረትም በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ሐምሌ 1 ቀን፣ 2015 (ሐምሌ 8 ቀን 2023)፣ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በኦሺንያ እና እስያ ከሚኖሩ ጋር ደግሞ በሐምሌ 2 ቀን፣ 2015 (ሐምሌ 9 ቀን 2023) የበይነ መረብ (ዙም) ስብሰባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ምዝገባው ከሰኔ 20 እስከ 29 ቀን 2015 ዓ.ም (ሰኔ 27-ሐምሌ 6 ቀን 2023) የሚካሄድ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ከስብሰባው አንድ ቀን በፊት የስብሰባው ሊንክ ተመዝጋቢዎች በመመዝገቢያው ቅፅ ላይ ባሰፈሩት የኢሜል አድራሻ እንደሚላክ ተጠቁሟል፡፡

የስብሰባዎቹ ሰዓት ለአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ለኦሺንያ እና እስያ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እና ለሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ አመሻሽ ላይ በ12 ሰዓት እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡