የሀረሪ ክልል በ50 ሚሊየን ብር ወጪ የወጣት ማዕከል ሊያስገነባ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – የሀረሪ ክልል ደረጃውን የጠበቀ የወጣት ማዕከል በ50 ሚሊየን ብር ወጪ ሊያስገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የግንባታ ስራውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ ወጣቶች በመልካም አስተሳሰብ፣ በክህሎትና እውቀት ታንፀው ራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

ወጣቱን ወደ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ማስገባትና ሀገራዊ ለውጡን ፍሬያማ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የወጣቶች ማዕከላትን በመገንባትና ግብዓት በማሟላት ውጤታማ ስራ ማከናወን ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሚገነባው ማዕከልም በክልሉ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ማዕከላት የተለየና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፣ በውስጡም የተለያዩ የመዝናኛ ማዕከላትን የያዘ ነው ብለዋል፡፡

ወጣቱ ማህበረሰቡንና ሀገሩን በመገንባት ሂደት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያስችላል ነው የተባለው፡፡

የሸንኮር አካባቢ ነዋሪም ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆን እንደከዚህ ቀደሙ ድጋፉን እንዲያጠናክር ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው፣ በክልሉ ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ የወጣት ማዕከል አለመኖሩን ጠቁመው፣ የሚገነባው ማዕከል የወጣቶችን ጥያቄ ከመመለስ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት የሚመለከታቸው አካላት በንቃት ማሳተፍ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከሀረሪ ክልል ኮሙዩኒኬሺን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የሸንኮር ወረዳ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ናስር መሀመድ በበኩላቸው፣ የክልሉ መንግስት በወረዳው ደረጃውን የጠበቀ የወጣት ማዕከል እንዲገነባ ለጀመረው ስራ ምስጋና አቅርበው ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብና በጥራት እንዲገነባ ወረዳው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡