የሀዋሳ አየር ማረፊያ ቢሻን ጉራቻ የመንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

ጥር 2/2014 (ዋልታ) የሀዋሳ አየር ማረፊያ ቢሻን ጉራቻ የመንገድ ግንባታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ፡፡

35 ኪ.ሜ የሚረዝመው የመንገድ ስራ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ የሀዋሳ ኤርፖርትን መዳረሻው ሰለሚያደረግ በዋናነትም ለሲዳማ እና ደቡብ ክልሎች የዓየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች የመንገዱ መገንባት ምቹ መሰረተ ልማትን ዕውን በማድረግ እስትራቲጂካዊ ጠቀሜታውን የጎላ አድርጎታል።

ለሀዋሳ ሀይቅ እና ለአካባቢው ተደራሽ በመሆኑ የቱሪዝም ፍሰትን እንዲጨምር በማድረግ ረገድም ሚና እንዳለው የተገለጸ ሲሆን በሀይቁ ውስጥ የሚገኘውን ከፍተኛ የዓሳ ምርት በአጭር ጊዜ ወደ ገበያ ለማውጣትም ያስችላል ተብሏል፡፡

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚመረቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የተለያዩ አልባሳትን መንገዱን በመጠቀም ወደ ሀዋሳ አየር ማረፍያ ለማድረስ እንደሚረዳ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የመንገዱ መገንባት ከዚህ ቀደም መንገድ ተጠቃሚውን ሕዝብ ይፈጠርበት የነበረውን ማኅበራዊ እንግልት በማስቀረት የተቀላጠፈ የትራንስፖርት ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል።

መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የወሰደውን 592 ሚሊዮን 84 ሺሕ ብር ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ ሲሆን የመንገዱን ግንባታ ዓለም ዐቀፉ የሥራ ተቋራጭ ቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ አከናውኖታል ተብሏል።