የሁለቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ በእንጅባራ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 7/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ በእንጅባራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
“የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለዘላቂ ሠላም” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው መድረኩ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል አፈ ጉባኤ ዓለምነሽ ይባስ ተገኝተዋል፡፡
በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የተለያዩ የጸጥታ ተቋማት አዛዦች እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መድረኩ የሁለቱን ክልል ሕዝብ የቆየ ትስስር እና አብሮነት የሚያንጸባርቁ የአማራ፣ አገው፣ የሽናሻ እና ጉሙዝ ሕዝቦች የተለያዩ የጥበብ ሥራዎች እየቀረቡ ነው፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በሁለቱ ክልሎች መካከል መልካም ግንኙነትን በመገንባት በጋራ ለመሥራት፣ ለማደግ እና በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያግዛል መባሉን አሚኮ ዘግቧል፡፡