የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ ይፋ ሆነ

ነሐሴ 25/2015 (አዲስ ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጋራ ፕሮጀክት የሆነው የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ ይፋ ሆነ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት የፋይናንስ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አተገባበር ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

በዕለቱ ይፋ የሆነው የመንግስት ዲጂታል የግዥ ካርድ ተቋማት የዲጂታል ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል ሲሆን የመንግስት ወጪ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እንደገለጹት የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ስርዓት በአጭር ጊዜ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝና በዚህም በበጀት ዓመቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ከ170 በላይ የሚሆኑ ተቋማት 3 ነጥብ 3 ትሪሊዮን በዲጂታል ግብይት በኩል ገንዘብ መንቀሳቀሱን ገልጸዋል።

የዲጂታል ግብይት ስርዓት ማለማመድ ረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖ ቢቆይም፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ በመንግስት ከመጣ በኋላ ትልቅ ለውጥና መነቃቃት አምጥቷል ብለዋል።

በዕለቱ ይፋ ከሆነው የመንግስት የግዥ ካርድ በተጨማሪ ሌሎች የክፍያ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮች እንደሚጀመሩ ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የግዥ ካርድ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸው በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ቁልፍ ዘርፍ የዲጂታል ሽግግር እውን ማድረግ መሆኑንና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ ብዙ ርቀት መኬዱን ተናግረዋል።

በመንግሥት የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ወደ ስራ የተገነባና የሕግ መሰረት ያለው የዲጂታል ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህም የመንግስት ክፍያ ስርዓትን በኤሌክትሮኒክ ግብይት ማስገባት አንዱና ዋነኛ ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የመንግስት ግብይት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስርዓት ትልቅ ድርሻ ስላለው ከባንኩ ጋር በጋራ የሚሰሩ ስራዎች ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ነው ያሉት።

የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ዕውን ማድረግ የክፍያ ስርዓትን ከማሻሻል ባለፈ የፋይናንስ ተጋላጭነት በመቀነስ በኩል ፋይዳው የጎላ ነው።

በሂደትም አጠቃላይ የዲጂታል ስርዓትን በማስፋፋት ይህ አገልግሎት ከሌሎች ባንኮች ጋርም ክፍያ መፈፀም የሚያስችል እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።

በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ ይገባል ያሉ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ወደዚህ ዘመናዊ አሰራር እንዲገቡ አሳስበዋል።

በበጀት ዓመቱ በዲጂታል አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው ተቋማት ዕውቅና መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።