የአየር ጠባይ ትንበያ በወቅቱ እና በብቃት እየደረሰ ነው – የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት

ነሐሴ 25/2015 (አዲስ ዋልታ) የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የአየር ጠባይ ትንበያን በወቅቱ እና በብቃት እያደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ በመጪው በጋ የሚኖረውን የአየር ጠባይ ትንበያ ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ እያደረገ ነው።

በመድረኩ በ2015 አመት በኢትዮጵያ ይኖራል ተብሎ የተተነበየው የአየር ትንበያ ምን ይመስል እንደነበር እየተገመገመ ነው።

በሀገሪቱ ያላትን ሶስት ወቅቶች መሰረት በማድረግ በተሰሩ ስራዎች የቅድመ አደጋ ስጋቶችን መቀነስ ስለመቻሉም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሜቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ኢንስቲትዩቱ ባለፈው ክረምት የሰጠው ትንበያ ሲገመገም ዝናቡ በትንበያው መሰረት በደቡብ ምእራብ አካባቢዎች ላይ ቀድሞ የጀመረ መሆኑና የዝናቡ መጠን እና ስርጭትም በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋና የተጠናከረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በ2016 የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛ በላይ የባህር ወለል መሞቅ እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ ከመደበኛ በላይ የባህር ወለል ሙቀት መጠን እንደሚሆን ትንበያው ያመላክታል ብለዋል።

በበጋ ወቅት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው እና የሚመለከታቸው ሴክተሮች ይሄንን መልካም እድል እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል ።

ኢንስቲትዩቱ ይፋ ካደረገው የበጋ ወቅት ትንበያ በተጨማሪ በየጊዜዉ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ የአየር ሁኔታዎችን አስቀድሞ በመተንበይ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መግለጫዎችን የሚሰጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይሄንን መረጃ እዲጠቀምና በቅርበት ክትትል እንዲያደርግ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

በስመኝ ፈለቀ