የምዕራብ ሀረርጌ አርሶአደሮች በመስኖ ስራ ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ አከባቢ አርሶአደሮች አዲስ በጀመሩት ስንዴን በመስኖ የማምረት ስራ ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ።

አርሶአደሮቹ ከዚህ ቀደም በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ማሽላ በማምረት ኑሯቸውን እንደሚመሩ እና ለከባድ የኑሮ ጫና ይዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል።

በወረዳው ሁሼ ዴራ ቀበሌ አርሶ አደሮች መንግስት እያደረገላቸው ባለው ሁለንተናዊ ድጋፍ በማህበር በመደራጀት በ40 ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር የመስኖ ስንዴ ማምረት መጀመራቸውን እና የውሃ እጥረት እንዳይኖርም የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው አየር ሁኔታ ሞቃታማና የዝናብ እጥረት ያለበት መሆኑን ተከትሎ የማሽላ ምርት ብቻ በአመት ያመርቱ እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደሮቹ፣ አሁን በተፈጠረላቸው ለውጥ ሌሎች ተጨማሪ ሰብሎችን በማምረት የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የወረዳው የግብርና ቢሮ ፅህፈት ቤት እና የአፈር ለምነት ጥበቃ ለአርሶ አደሮቹ  ከሰው ሰራሽ ማዳበርያ ባሻገር የተፈጥሮ ማዳበርያ ወይም ኮምፖስት ፋርም እንዲጠቀሙ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አስታውቋል።

ይህም አርሶአደሩ በስፋት ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ የማዳበርያ እጥረትና ከፍተኛ ወጭን ለመቀነስ አስተዋፅኦ እንዳለው ተመላክቷል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)