የረመዳን ፆም ነገ ይጀመራል

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – የ1442ኛው የረመዳን ፆም ነገ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል እንዳረጋገጠው፣ ጨረቃ ዛሬ በመታየቷ ህዝበ ሙስሊሙ በፆምና ጸሎት የሚያሳልፈው የረመዳን ወር ነገ ይጀምራል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ባለፈው ሳምንት የረመዳን ጾም መቃረብን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ጾምን በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመተዛዘንና መልካም ተግባራትን በማከናወን እንዲያሳልፍ አሳስበዋል።

ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ “ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳንን ጾም በሚጾምበት ጊዜ ለሰዎች እያዘነና እየተረዳዳ ሊያሳልፍ ይገባል” ብለዋል፡፡
በጾም ወቅት በጎ ተግባራትን ማከናወን ጾሙ ትክክለኛና በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኝም ገልጸዋል።
(ምንጭ፡-ኢዜአ)