ጠንካራ የዲጂታል መረጃ ፍሰትን ለመፍጠር እየተሰራ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት


ጥቅምት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) አሁን ያለውን የዲጂታል አለም ፍጥነት ያገናዘበ የመንግስት የመረጃ ፍሰትን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህን ያሉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመሆን ለሚያሰራው የመረጃ ዌብ ፖርታል የስምምነት ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት ነው።

ዌብ ፖርታሉ የሃገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃንና ማንኛውም መረጃ ፈላጊ በሙሉ የመንግስትን እቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ተግባራትን የተመለከቱ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የሚያስችለው እንደሚሆን ተገልጿል።

ከአገልግሎቱ መረጃዎችም ባሻገር የፌደራልና የክልል ኮሙኒኬሽን ተቋማት መረጃዎቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበትን አሰራር አካቷል።

የዲጂታል ፕሮጀክቱን እየሰራ የሚገኘው የኢንፎርሜሸን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ አርአያስላሴ እንዳሉት አዲስ የሚለማው ዌብ ፖርታል ለመረጃ ፈላጊዎች በቀላሉ መገኘት እንዲችል፣ ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆንና በውስጡም የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን እንዲይዝ ይደረጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ዜጎች በተለያዩ የመንግስትና የክልል ቋማት ላይ ያላቸውን ጥያቄ፣ አስተያየትና ቅሬታ የሚያቀርቡበትንም አሰራር የያዘ መሆኑ በስምምነቱ ወቅት መገለጹን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዌብ ፖርታል በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ስራው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል።