የስራ ባህሉ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርብ የመገናኛ ብዙኃን ሚና የጎላ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

ኅዳር 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የስራ ባህሉ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርብ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሚና የጎላ ሊሆን እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዙርያ “ክህሎት ለሁለንተናዊ ስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ ለመገናኛ ብዙኃን አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ዘርፉ ለሀገራዊ ልማትና ብልፅግና ያለውን አበርክቶ ሊያሳድጉ የሚችሉ አዳዲስ እሳቤዎችን ቀርፆ ወደ ስራ ማስገባቱን አንስተዋል።

ሀገራዊ የልማት ግቦች እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ በየደረጃው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ውጥን መያዙን ገልጸዋል።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሀመድ ሀሰን

ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በሚሰጠው የተዛባ እይታ ሳብያ የቴክንክና ሙያ ስልጠናን ምርጫቸው አድርገው የሚመጡ ዜጎች መጠን ውስን መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ ከዘርፉ ገፅታ ግንባታ አንፃርም ሆነ እንደ ሀገር የስራ ባህሉ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርብ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ሚና የጎላ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያደገችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት ይሻል ያሉት ሚኒስትሯ ይህን መሻት ለማሳካትና የሀገርን የተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ ለስራና ክህሎት ልዩ ትኩረት ሰጥተን በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

የሚዲያ ተቋማት በህብረተሰቡ ዘንድ በሙያና ሙያተኛ፣ በስራ ባህል እንዲሁም ስለ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ያለውን አሉታዊ አስተሳሰብ የሚቀይሩና የባህሪ ለውጦችን የሚያመጡ ስራዎችን እንዲሰሩም መድረኩ አጋዥ መሆኑ ተጠቁሟል።

መድረኩን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ኢኒስቲትዩት እንዲሁም ከመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ጋር ያዘጋጀ ሲሆን ዋልታ ሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት በጋራ ማዘጋጀቱም ተመላክቷል።

በታምራት ደለሊ