5ኛ ትውልድ ኔትወርክ ለጤናው ዘርፍ የሚኖረው ቱርፋት

አምስተኛ ትውልድ ኔትወርክ (5G network) የሚባለው እጅግ ፈጣን የገመድ አልባ ኔትወርክ ሲሆን ትልቅ መጠን ያላቸውን መረጃዎች በፍጥነት ለመለዋወጥ ያስችላል፡፡ ይህ በዓለም እየተስፋፋ የመጣው አዲሱ ትውልድ ኔትወርክ ከፍተኛ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እምርታ እንደሚያመጣ የሚጠበቅ መሆኑ ይነገራል፡፡

ኔትወርኩ ስማርት የሚባሉ እንደ ስልክ፣ ቴሌቪዥን፣ መኪና፣ ማቀዝቀዧ፣ ሰዓት፣ ልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የህክምና የመከታተያ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው በማገናኘት መረጃ እርስ በርስ እንዲለዋወጡ ያደርጋል።

በረካታ የዓለም ሀገራት ይህን ፈጣን ኔትወርክ ስራ ላይ እያዋሉ ሲሆን በአፍሪካም ኢትየጵያን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሸልስ፣ ቦትስዋና፣ ሞሪሽየስ፣ ዚምባብዌ፣ ቶጎ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጀሪያ የመሳሰሉት ሀገራት ተግባራዊ አድረገዋል፡፡

አምስተኛው ትውልድ ኔትወርክ በህክምናው ዘርፍ ሰፊ ድጋፍና አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጅምር ተግባራት እየታዩ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ይህ አዲሱ ትውልድ ኔትወርክ እንዴትና በምን መልኩ ለጤናው ዘርፍ ተጨባጭ እምርታ ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ጥቂት ምሳሌዎችን በማንሳት እንመልከት፡፡

ታማሚን በርቀት ለመቆጣጠር ይረዳል

5ኛ ትውልድ ኔትወርክ ታካሚን ማዕከል ያደረገውን የህክምና አሰጣጥ ስርዓት ያዘምነዋል፡፡ ኔትወርኩ እጅግ ፈጣን በመሆኑ በቪዲዮ የሚተላለፍ መልዕክት ከመነሻው እስከ መድረሻው የሚኖር የጊዜ ልዩነት በማጥፋት ቀጥታ ታማሚን ለመከታተል ያስችላል፡፡

ይህ ኔትወርክ ሰዎች በሚጠቀሟቸው እንደ እጅ ሰዓትና በመሳሰሉ የመከታተያ መሳሪያዎች መረጃ በመሰብሰብ ለሃኪሞች የተሻለ መረጃ በማቅረብ ቅድመ ዝግጅትና ውጤታማ ህክምና እንዲሰጡ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

እድሜያቸው ለገፋና ከቤታቸው ወጥተው መታከም ለማይችሉ ታካሚዎች፣ በሞቀ ቤታቸው ሆነው ክትትልና እንክብካቤ እንዲያገኙ ይህ የአዲሱ ትውልድ ኔትወርክ አይተኬ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡

በሮቦት የተደገፈ ቀዶ ጥገና ለማድረግ

አምስተኛ ትውልድ ኔትወርክ የሚጠቀም ሮቦት ከህይወት ድጋፍ ማድረጊያ የህክምና መሳሪያዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በርቀት ያለን ታማሚ ቀዶ ጥገና በማድረግ ፈውስ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ በፈረንጆቹ 2019 የ5ኛ ትውልድ በሮቦት የተደገፈ ቀዶ ጥገና በእንስሳት ላይ ተሞክሮ ውጤቱ አስደሳች እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

ለአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት

ሩቅና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች አፋጣኝ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ህይወት ለማትረፍ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና መድኃኒቶችን ለማድረስ አምስተኛው ትውልድ ኔትወርክ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ነው የተገለጸው፡፡

አምስተኛ ትውልድ ኔትወርክ የሚጠቀሙ ድሮኖችን በመጠቀም ለመሄድ አስቸጋሪ ወደ ሆኑ ቦታዎች አስፈላጊ የህክምና ግብዓቶችን ለማድረስ ጥቅም ላይ ውሏዋል፡፡ በኮሮና ወቅት የምርመራ ናሙናዎችን፣ ክትባቶችን እንዲሁም በአደጋ ምክንያት ደምና የአካል ክፍል ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በፍጥነት ለመላክ ፈጣን አገልገሎት በመስጠት ፋይዳውን አስመስክሯል፡፡

አምሰተኛ ትውልድ ኔትውርክ የህክምና ስህተትን ለማስቀረት ያግዛል

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሙሉ አቅሙ ውጤታማ የሚሆነው በ5ተኛ ትውልድ ኔትውርክ ሲደገፍ ነው፡፡ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Ai) በተለይም ደግሞ መረጃ አመንጪ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (generative AI or GenAI) የሚባለው ለህክምው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የተጠየቀውን መረጃ በፅሁፍ፣ በፎቶ ወይም በድምፅ ወምስል አዘጋጅቶ ምላሽ ለመስጠት 5ተኛ ትውልድ ኔትውርክን መጠቀም የግድ ይለዋል፡፡

ይህ በህክምናው ዘርፍ የአንድ በሽታን ምርመራ ውጤት በማብራራትና የታካሚውን ልዩ ሁኔታና ባህርይን መሰረት አድርጎ ምክረ ሃሳብ (personalized recommendation) ለመስጠት ይጠቅማል። በአሜሪካ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰዎችን ዘረመል በመተንተን ካንሰርን መመርመርና ለታካሚው ልዩ ማንነት የተቀመመ ህክምና (tailored treatment) የማድረግ ተግባራት ስራ ላይ መዋል ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡

በሽታን ቀድሞ ለመተንበይ

ስልካችን፣የምናስረው ሰዓት፣ኮምፒውተራችን፣ስማርት ቴሌቪዥናችን ወዘተ ስለኛ እያንዳንዷን ነገር ይመዘግባል፣ ያውቃል፡፡ ስንት ሰዓት እንደሮጥን፣ ስንት ኪሎሜትር በእግራችን እንደሄድን፣ ለስንት ሰዓት እንደምንተኛ፣ ምን ያህል ጊዜ ተቀምጠን እንደነበር፣ የልብ ምታችንን፣ ምን ያህል ካሎሪ እንዳቃጠልን፣ ምን ምግብ አዘውትረን እንደምንገዛና እንደምንመገብ ወዘተ መረጃ ይሰጠናል፡፡ ይህ የሚሰበሰበው መረጃ ስለ ህይወት ዘያችን (lifestyle) ብዙ ይናገራል፣ የጤና ሁኔታችንን ለመተንበይ ይረዳል ማለት ነው፡፡

የ5ተኛ ትውልድ ኔትወርክን ከረቀቁ የቴክኖሎጅ ውጤቶች ጋር በማጣመር የጤና ስርዓታችንን እና የህክምና አገልገሎት ጥራትና ስርጭትን ለመጨመር አይተኬ ሚና ይኖረዋል፡፡ ጤናችሁ ይብዛ!

ምንጭ፣የተለያዩ የህክምና ድረ-ገጾች

በቴዎድሮሰ ሳህለ