የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ በዚህ ዓመት ስራ ይጀምራል

 

እየተገነቡ ካሉ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ በዚህ ዓመት ስራ እንደሚጀምር ተገለጸ።

ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ መንግስት እየተገበራቸው ከሚገኙ ተግባራት ውስጥ አንዱ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት መሆኑ ይታወቃል።

በኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የቡልቡላ ፓርክ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮሀንስ መኮንን ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም በከፊል ምርት ማምረት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የፓርኩ ግንባታ ደረጃ ምዕራፍ ሙሉ በመሉ፣ ምዕራፍ ሁለት 87 በመቶ እንዲሁም ምዕራፍ ሦስት 75 በመቶ መጠናቀቁን አቶ ዩሐንስ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሸካ ሞርዲ የተባለ የማር ማቀነባበሪያ ድርጅት ገብቶ የማሽን ተከላ ስራውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን የገለጹት ሃላፊው የውሃ አቅርቦት፣ የትሪትመንት ፕላንት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አለመሟላት ምርት ወደ ማምረት ተግባር እንዳይገባ ትልቅ ችግር እንደሆነበትም ነው የተናገሩት ።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ – ኢንዱስትሪ ፓርክና የኢንዱስትሪ ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አያልነህ አባዋ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም በዚህም በአጭር ጊዜ ችግሮቹ ተቀርፈው ባለሃብቶች ወደ ማምረት ሂደት እንደሚገቡ አስረድተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የውጪ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

በተጨማሪም ባለሀብቶች በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ መዋዕለ-ነዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ እራሳቸውን ብሎም ሃገራችውን እንዲጠቅሙ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።