የቤተሰብ ሕጎች የሴቶችን እና የሕጻናትን ሰብአዊ መብቶች ከማስከበር አኳያ ሊፈተሹ ይገባል – ኢሰመኮ

ግንቦት 24/2013 (ዋልታ) – የፌዴራል እና የክልል የቤተሰብ ሕጎች የሴቶችን እና የሕጻናትን ሰብአዊ መብቶች ከማስከበር አኳያ በየጊዜው ሊፈተሹ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው እ.ኤ.አ በየዓመቱ ጁን 1 የሚታሰበውን ዓለምአቀፍ የወላጆች እና አሳዳጊዎችን ቀን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።
የዘንድሮው የወላጆች እና አሳዳጊዎች ቀን “ምስጋና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወላጆች እና አሳዳጊዎች” በሚል መሪ ቃል ነው የተከበረው፡፡
የፌዴራልም ሆነ የክልል የቤተሰብ ሕጎች የሴቶችን እና የሕፃናትን መብቶች ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም፣ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎች እና ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረሱ ከሆነ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለድርብ ተጋላጭነት ሊዳርጉ የሚችሉ መሆኑ በመግለጫው ተገልጿል።
የሕፃናትን ስብእና በማነፅ እና ሰብአዊ ክብርን በማስተማር ረገድ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወስዱ ለማስታወስ እና ተገቢውን ዕውቅና ለመስጠት በተመድ የተሰየመው ይህ ቀን በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የወላጆች እና የአሳዳጊዎች ሚና ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉ እየተገለጸ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
በሀገር አቀፍ ደረጃም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በግጭቶች እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ምክንያት ለተለያዩ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረጉ ሕፃናት እና አሳዳጊዎች መኖራቸው፣ በእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሕጎች እና ፖሊሲዎችን ወቅታዊነት እና አግባብነት ዳግም ለመፈተሽ የሚያስገድድ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሷል።
በመሆኑም የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ዲፓርትመንት በ2014 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚያከናውነው የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የአተገባበር እና የመዋቅር ማሻሻያዎች ምክረ-ሐሳብ እና ግፊት ሥራ ካቀዳቸው ዋና ዋና መስኮች አንዱ የፌዴራል እና የክልል የቤተሰብ ሕግ መሆኑን ገልጿል።