ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ10 አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

ግንቦት 24/2013 (ዋልታ) – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና እስያ አገሮች አዲስ የተመደቡ የአስር አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ።
ፕሬዚዳንቷ በኢትዮጵያ የካናዳ፣ የእስራኤል፣ የባንግላዴሽ፣ የሞዛምቢክ፣ የናይጄሪያ፣ የሶማሊያ፣ የቤላሩስ፣ ቬትናም፣ ቤኒን እና ኢስቶኒያ አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ነው የተቀበሉት።
የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዚዳንቷ ያቀረቡት የካናዳው አምባሳደር ስቴፋኒ ጆኒንና የእስራኤሉ አምባሳደር አሌሊ አድማሱ በአገራቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ያላት እንደመሆኑ ግንኙነታቸው የሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የሶማሊያ አምባሳደር አብዱላሂ አህመድ ጀማ፤ በአገራቱ መካከል የነበረውን ወዳጅነት ለማጠናከር እንደሚተጉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ወደ 2 ሺህ ገደማ ኪሎ ሜትር ድንበር የሚጋሩና በርካታ የሚያስተሳስራቸው ጉዳይ መኖሩን አውስተዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት አምባሳደሮች ከፕሬዚዳንቷ ጋር በነበራቸው ውይይት ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ ጠንካራ ወዳጅነት ለመፍጠር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ብለዋል።
ለአምባሳደሮቹ በኢትዮጵያና በአካባቢው ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ማብራሪያ መሰጠቱንም ኢዜአ ዘግቧል።