የቻይና ከፍተኛ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ማዕቀብን ለመከላከል የሚያስችል ድንጋጌ አሳለፈ

ሰኔ 07/2013 (ዋልታ) – የቻይና ከፍተኛ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ማዕቀብን ለመከላከል የሚያስችል ድንጋጌ አሳለፈ።

የአገሪቱ ከፍተኛ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ለማስቻል ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ፊርማቸውን አኑረውበታል።

በኢትዮጵያ የቻይና ሪፐብሊክ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ቻይና በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ጠንካራ መርህ አላት።

ይህ የቻይና መርህ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ቻርተር የተቀመጠና የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ኤምባሲው ገልጿል።

አገሮችም ይህንን መርህ ከግምት አስገብተው እንደሚንቀሳቀሱ አውስቷል።

ነገር ግን ከቅርብ አመታት ወዲህ የምዕራባውያን አገሮችና ድርጅቶች የቻይናን የአገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲ እንደሚያብጠለጥሉና ማዕቀብ እየጣሉም እንደሆነ አመልክቷል።

ለአብነትም የዢንጂያንግ፣ ቲቤትና ሆንግ ኮንግ ጉዳዮችን አንስቷል መግለጫው።

እንዲህ አይነቱን የበላይነትን ይዞ ለመቆየት የሚደረግን ጥረት የቻይና መንግስት በጽኑ እንደሚያወግዝ ያመለከተው መግለጫው፤ በሁሉም ዘርፍ የሚገኘው የቻይና ህዝብ ይህንን ያልተገባ ጫና እንደሚያስቆጣው ገልጿል።

ብሔራዊ ሉዓላዊነቱን፣ ክብሩን፣ ዋና ዋና ጥቅሙን ለማስጠበቅና የምዕራባውያንን የበላይነት የማስጠበቅ ጥረትና የሃይል ሚዛንን የመቆጣጠር ፖለቲካን ለመከላከል የቻይና መንግስት በርካታ ጥረት ማድረጉን አስታውሷል።

እ.አ.አ በ2021 መጀመሪያ ጀምሮ በአገሮች ላይ የሚደርሰውን ያልተገባ ጫናን ለመከላከል እየሰራ እንደሚገኝም ኤምባሲው አመልክቷል።

በዚህ ረገድ የውጭ ማዕቀብን ለመከላከል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ ቻይና ህጉን ልታወጣ እንደቻለች ጠቅሷል።

በህጉ የውጭ ማዕቀብን ለመከላከል የሚያስችሉ ሶስት ጉዳዮች መካተታቸውን ያመለከተው የኤምባሲው መግለጫ፤ ቪዛ መከልከል፣ ወደ ቻይና መግባትን ማገድ፣ የቪዛ ማምከንና ከአገር ማባረር አንዱ ጉዳይ እንደሆነ አመልክቷል።