የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ማስጀመሪያ ስምምነት ተደረገ

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

ግንቦት 27/2013 (ዋልታ) – በስልጤ ዞን ስልጤ ወረዳ የመናሃሪያ ከተማ ለ20 ዓመታት የማህበረሰቡ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስምምነት ተደርጓል።

ለፕሮጀክቱ 19 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጭ የሚደረግ ሲሆን፣ እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ የቁፋሮ ስራውን በማካሄድ በሚቀጥለው በጀት አመት የመስመር ዝርጋታው ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

በስምምነት መርኃግብሩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የስልጤ ማህበረሰብ ጠንካራ ሰራተኛ እና ሠላም ወዳድ መሆኑን ጠቁመው፣ መንግሥትም የማህበረሰቡን ችግር ደረጃ በደረጃ እየፈታ ነው ብለዋል።

መንግሥት በሀገሪቱ የሚታየውን የጸጥታ ችግር በመቅረፍ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትና ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ዘብ ሊቆም እንደሚገባም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ማህበረሰቡ በየጊዜው የሚያነሳቸውን የመልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ተጀምረው የሚጓተቱ እንዲሁም አዳዲስ የሚጀመሩ ፕርጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

በተጨማሪም በወረዳው ግንባታቸው የተጠናቀቁ ድልድዮችና የገን ስልጤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ ክፍሎች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

(በምንይሉ ደስይበለው)