የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ባለፉት አምስት ዓመታት ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ስኬታማ እንደነበር ተገለጸ


ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ባለፉት አምስት ዓመታት ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ስኬታማ እንደነበር የወቅቱ የኢኒሼቲቩ ሊቀ መንበርና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ ስብሰባ ጎን ለጎን 20ኛውን የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ የመሩ ሲሆን የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ በስብሰባው ተገኝተዋል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄዳው ስበሰባ የአፍሪካ ቀንድ የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የዓለም ባንክ ተወካዮች እንዲሁም የጀርመን እና ብሪታኒያ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በ20ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ የአረብ ባንክ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት፣ የሳዑዲ ልማት ፈንድ፣ የአሜሪካ እና የጃፓን ልዩ መልዕክተኛ በአጋርነት መሳተፋቸውም ተመላክቷል፡፡

አዳዲስ ተቋማት በኢኒሼቲቩ መሳተፋቸውን ያደነቁት ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ ባዘጋጀው ህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ተካተው መደበኛ አጋር እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢኒሼቲቩ ባለፉት አምስት ዓመታት ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ስኬታማ እንደነበር አስታውሰው ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ኢንሼቲቭ ሰባት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በአባልነት አካትቶ በፈረንጆቹ 2019 የተመሰረተ ሲሆን በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡