የአረብ ሊግ የህዳሴን ግድብ በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የሌውም- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሰኔ 09/2013 (ዋልታ) – የአረብ ሊግ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ በኳታር ተወያይቶ ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአረብ ሊግ የግብጽ እና የሱዳንን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ላይ ሳይመሰረት በህዳሴ ግድቡ ድርድር ዙሪያ ገንቢ ሚና መጫወት ሲገባው ሚዛናዊነት የጎደለው እና ወደ አንድ ወገን ያደለ ውሳኔ መወሰኑ ተቀባይነት እንደሌለው ነው መንግስት ያሳወቀው፡፡

ውሳኔው በቀጠናው የዓባይን ወንዝ በትብብር እና በዘላቂነት ለመጠቅም የሚያስችል መንገድ አለመሆኑንም ገልጿል፡፡

የአርብ ሊግ አባል ሀገራት የዓባይ ወንዝን አጠቃቀም እና የኢትዮጵያን ነባር አቋም በሚገባ ሊያውቁ ይገባቸዋልም ብሏል፡፡

የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከድህነት የምታወጣበት የሀይል አቅርቦት እና የምግብ ዋስትና የምታረጋግጥበት ፕሮጅክት በመሆኑ የህልውናዋ ጉዳይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ነው ያለው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የውሃ አጠቃቀም ህግን በማክበር የተፈጥሮ መብቷን እየተጠቀመች መሆኗም ሊታወቅ ይገባል ብሏል፡፡

ዓባይ የጋራ ሀብት እንጂ የተናጠል የግብጽ እና የሱዳን ብቻ አይደለም ነው ያለው መግለጫው፣ የተፋሰሱ ሀገራት በትብብር እና በውይይት መስራት የውሃ ደህንነትን ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ እንደሆነ የኢትዮጵያ ጽኑ እምነት እንዳላት አስታውቋል ነው፡፡

የአረብ ሊግ ሚዛናዊነት የጎደለው ሌሎች የዓባይ ባለቤት የሆኑ የተፋሰሱን ሀገራት ወደ ጎን በመተው ለሁለቱ ሀገራት ብቻ ያደላ አወዛጋቢ አቋም መያዙ የሚኮንነውም ለዚሁ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ስጋት ግምት ውስጥ ያስገባ፣ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራትን በጋራና በትብብር መንፈስ እንጠቀም መርህን ተግባራዊ ታደርጋለች፡፡

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገውን ድርድር በሚገባ ሳያጤኑ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ያሳለፉትን ውሳኔ ዳግም ያጤኑታል የሚል እምነት ኢትዮጵያ እንዳላትም አስታውቋል፡፡

የህዳሴውን ግድብ አሞላልን በተመለከተ ሊጉ የያዘውን አቋም የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡

ከዚህ ይልቅ እንደ አንድ የቀጣናው ድርጅት፣ ሶስቱ ሀገራትን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ በማምጣት የተዛባ እና ምክንያታዊ ያልሆነ አቋሙን እንዲያስተካክል መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡