የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሰነድ ለሕዝብ ሊሠራጭ ነው

የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሰነድ

ሚያዝያ 01/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ኮሚሽን ያዘጋጀው የአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሰነድ በሚቀጥለው ሳምንት ለሕዝብ እንደሚሰራጭ ተገለጸ፡፡

በቀጣዩ ሳምንት ለሕዝብ እንዲደርስ የተሰናዳው የልማት እቅድ ‹ሶፍት ኮፒ› በዋነኝነት በፕላን እና ልማት ኮሚሽን ድረ ገጽ ይለቀቃል ነው የተባለው።

በተጨማሪም በኮሚሽኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ማግኘት እንደሚቻል ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል በመጽሐፍ መልክ የተሰናዳው ሰነድ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኅትመት ሒደት ላይ እንደሚገኝ እና የኅትመት ሒደቱ ሲጠናቀቅ ለሕዝብ እንደሚሠራጭ ኮሚሽኑ ለዋልታ በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡

የልማት ዕቅድዱ በኢትዮጵያ በቀደሙ ዓመታት የልማት ዕቅድ ትግበራ ክፍተቶችን እንዲሁም የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን ከግምት በማስገባት በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ እንዲረዳ እና የተቀመጠውን ኢትየጵያን ‹‹አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት›› የማድረግ ሀገራዊ የልማት ርዕይ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የ10 ዓመታት የልማት ዕቅዱ ባሳለፍነው መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁ የሚታወስ ነው፡፡