የአውሮፓ ሕብረትና ዩናይትድ ኪንግደም በአዲሱ ዓመት በይፋ ተለያዩ

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግባቱን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የነበራትን ግንኙነት በይፋ አቋርጣለች።

ዩናይትድ ኪንግድም (ዩኬ)፤ ሐሙስ ለአርብ አጥቢያ በጂኤምቲ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 5 ሰዓት [በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ደግሞ ከሌሊቱ 8 ሰዓት] ጀምሮ የአውሮፓ ሕብረት ሕግጋትን መከተል አቁማለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዩኬ “ነፃነቷን በእጇ” ይዛለች ሲሉ ተደምጠዋል።

አሁን ነገሮችን “በተለይ መልኩና በተሻቀለ ሁኔታ” ማከናወን እንችላለን ሲሉም አክለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ዩናይትድ ኪንግደም “የሕብረቱ አጋር እና ጓደኛ ሆና ትቀጥላለች” ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ሕዝብ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያለን ግንኙነት ይብቃን ሲል በሕዝበ ውሳኔ ፍላጎቱን ያሳወቀው በፈረንጆቹ 2016 ነበር።

ነገር ግን ‘ብሬግዚት’ በተሰኘ ቅጥያ ስሙ የሚታወቀው ይህ ሂደት ከሦስት ዓመታት ውይይት በኋላ ተግባራዊ ሆኗል።

ላለፉት 11 ወራት ሁለቱ አካላት እየተወያዩ ባሉበት ወቅት ዩኬ ለሕብረቱ የንግድ ሕግጋት ተገዢ መሆን ነበረባት።

አሁን ዩናይትድ ኪንግደም 27 አገራት ካሉበት የአውሮፓ ሕብረት ሙሉ በሙሉ መውጣቷን ቢቢሲ ዘግቧል።