የኮሚሽነሮች ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ስራውን ጀመረ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በጸደቀው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1224/2012 መሠረት፤ የኮሚሽነሮች ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ  ስራውን ጀምሯል፡፡

በዚህ የኮሚሽኑን ምክትል ዋና ኮሚሽነር እና የልዩ ልዩ ዘርፍ ጉዳዮች ኮሚሽነሮችን ለመምረጥ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የሕዝብ እንደሚቀበል ተገልጿል፡፡

በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የልዩ ልዩ ዘርፍ ጉዳዮች ኮሚሽነሮች ማለት የሴቶችና ሕጻናት መብቶች ጉዳይ፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጉዳይ፣ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ጉዳይ፣ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መብቶች ጉዳይ እንዲሁም የስደተኞች፣ የተፈናቃይ ሰዎችና ሌሎችም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ የሚጨምር እንደሆነ ተጠቁሟለወ፡፡

ለኮሚሽነርነት የሚያበቁ መመዘኛዎች፡-

  • የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ/ያልሆነች፣
  • በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነ/የሆነች፣
  • ለሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ የሆነ/የሆነች እና በሰብአዊ መብቶች ሥራ ወይም ጥናትና ምርመር አስተዋጽኦ ያደረገ/ያደረገች፣
  • የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የሚያከብር/የምታከብር፣
  • በሕግ ወይም ተዛማጅነት ባለው ሌላ ሙያ የሰለጠነ/ች ወይም ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያካበተ/ያካበተች፣
  • ዕድሜ ከ 35 ዓመት በላይ የሆነ/የሆነች፣
  • በታታሪነት፣ በታማኝነት፣ እና በሥነ ምግባር በሕዝብ ዘንድ ወይም በአካባቢው ነዋሪዎች ወይም በስራ ባልደረቦች ዘንድ መልካም ስም ያተረፈ/ያተረፈች፣

ሲሆኑ የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው በሕዝብ ጥቆማ ከቀረቡት ሰዎች ውስጥ በተቻለ መጠን የልዩ ልዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች እና የጾታ ስብጥርን ከግምት በማስገባት፤ መስፈርቱን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟሉ ዕጩዎችን መርጦ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርብ መሆኑን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡