24ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 24ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

  1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከጣሊያን መንግስት ጋር በተፈረሙ ሶስት የብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ብድሩም የመንግስትን ልማት ተኮር እቅዶች ለመደገፍ የሚውል የ56 ሚሊየን ዩሮ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮን ዩሮው የቡና እሴት ሰንሰለት ለማሻሻል ለተቀረጸው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይውላል፡፡ 22 ሚሊዮን ዩሮው በገጠራማ አካባቢዎች የስራ እድል ፈጠራን በማሳደግ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፋን ለመደገፍ የሚውል ነው፡፡ ቀሪው 24 ሚሊዮን ዩሮ በአዋሽ እና በዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ዘላቂ የውሃ ሃብት ልማት እና አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት ይውላል፡፡ ምክር ቤቱም ሁሉም ብድሮች ከወለድ ነፃ መሆናቸው፣ የ16 ዓመታት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ30 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ መሆኑ ከአገሪቱ የብድር ፖሊሲ ጋር እንደሚጣጣሙ በማረጋገጥ ስምምነቶቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

 

  1. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከአለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር በተፈረሙ ሁለት የብድር ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የሁለቱ ስምምነቶች መጽደቅ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚውል የ250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደዚሁም የሰው ሀብት ልማት ሴክተር አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ ለመደገፍ የ50 ሚሊየን ዶላር ብድር ሚያስገኝ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱም ሁለቱም የብድር ስምምነቶች ከወለድ ነፃ ሆነው ማህበሩ ብድሩን በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልባቸው፣ የ6 ዓመታት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆናቸው ከአገሪቱ የብድር ፖሊሲ ያገናዘቡ መሆኑን በማረጋገጥ ስምምነቶቹን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

 

  1. በተጨማሪም የውጪ ግንኙነት ከማሳለጥ አንጻር የቀረቡ አጀንዳዎችም ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከሩሲያ ፌደሬሽን መንግስት ጋር በወታደራዊ-ቴክኒካል ትብብር ወቅት ለሚገኙ አዕምሯዊ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች የጋራ ጥበቃ ለማድረግ የተፈረመው ስምምነት ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ ነው፡፡ የስምምነቱ አላማ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ያለውን ፍላጎት በድጋሚ ማረጋገጥ፣ በሁለትዮሽ ወታደራዊ-ቴክኒካል ትብብር ሂደት በአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ መስክ የተሻለ የጋራ መግባባት እና ትብብር እንዲኖር ማድረግ፣ እንዲሁም በትብብር ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአእምሯዊ ንብረትን መብት ጥሰቶችን በጋራ መከላከል ሲሆን ምክር ቤቱም ስምምነቱ የእኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎችን መሰረት በማድረግ የተፈረመ መሆኑን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

 

  1. ምክር ቤቱ በአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት ላይ የተወያየ ሲሆን የአባል ሀገራትን የመድኃኒት ምርቶችን ጥራት ማስጠበቅ፣ ሀገራችን ከመድኃኒት ምርቶች ቁጥጥር ጋር ተያይዞ እያደረገች ያለውን ጥረት በማገዝ የመድሃኒት ጥራት ተቆጣጣሪ አካላትን አቅምና ብቃት ማሳደግ፣ የሀገራችንን ባህላዊ መድሃኒቶች ከዘመናዊው የህክምና ስርዓት ጋር ማስተሳሰር እንደዚሁም በአባል አገራት መካከል የመድሃኒቶች ዝውውር ቅንጅታዊ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት የኤጀንሲው ዋነኛ ተግባራት መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ምክር ቤቱም በስምምነቱ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

 

  1. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት ጉዳይ ከሊባኖስ መንግስታት ጋር በስራ ስምሪት ዘርፍ ስምምነት ነው፡፡ ሀገራችን በሊባኖስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ ያላት በመሆኑ የእነዚህን ዜጎች መብት ለማስጠበቅ ብሎም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ለማጠናከር እንደሚረዳ የታመነበት ስምምነት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም የስምምነቱ መፈረም በሊባኖስ በተለያዩ ስራ መስኮች ተሰማርተው ለሚገኙ እና ለወደፊትም በስራ ምክንያት ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል፣ የመብት ጥሰቶች በሚያጋጥሙ ጊዜም በአገሪቱ ህግ አግባብ እንዲዳኙ የሚያስችል እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስትም ለዜጎቹ ተገቢውን የህግ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለው ስምምነት መሆኑን በማረጋገጥ ግብዓቶችን በማከል እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

 

  1. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው ከደቡብ ኮሪያ እና ከህንድ መንግስታት ጋር የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት በተፈረሙ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ የሀገራቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና ዜጎች ለሥራ ጉዳይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን በማድረግ በተለይም ቪዛ ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀረት የጎላ ፋይዳ እንዳለው የታመነበት ስምምነት ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በስምምነቱ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

 

  1. በመጨረሻ ምክር ቤቱ ከፓኪስታን መንግስት ጋር በተፈረመው የንግድ ስምምነት ላይ የተወያየ ሲሆን የስምምነቱ መጽደቅ አገራቱ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸው መልካም ግንኙነት ብሎም በዓለም አቀፍ መድረኮች የጋራ አቋሞችን በማራመድ ረገድ ያላቸው ትብብር እንደሚያጎለብት የታመነበት ስምምነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በስምምነቱ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡