የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉንና የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ዛሬ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢዋን ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

በውይይታቸውም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት፣ የሁለቱ ሀገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት የሚሉት በሰፊው ተዳሰዋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት በተስማሙት መሰረት በትምህርት፣ በስልጠና እንዲሁም በተሞክሮና ልምድ ልውውጥ አብሮ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት መደረጉን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የልኡካን ቡድን ውጤታማ ቆይታ አድረጎ መመለሱም የዚህ ስምምነት አካል እንደሆነ አንስተዋል።

በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቶች በተመሳሳይ የስልጠና እና የልምድ ልውውጥ መርኃ ግብሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢዋን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው ይህ ግንኙነት በፓርቲ ለፓርቲም ሆነ በመንግስታዊ ወዳጅነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከፓርቲው የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።