የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

የካቲት 11/2016 (አዲስ ዋልታ) 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት የበለጠ ለማጠናከር፣ የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ ግብረ-ኃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር በመስራቱ ለተገኘው ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሏል መግለጫው።

ለጉባኤው የመጡ እንግዶች በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እጀባና ጥበቃ ማድረጉን የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ መሪዎቹም በሰላም ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በግብረ-ኃይሉ የተሠራው ፀጥታ የማስከበር ተግባር አፍሪካን ሊወክል እና ሊያኮራ የሚችል በመሆኑ ሀገራችን የአፍሪካ ኅብረትን ለማጠናከር ያላትን ሚና እንዲሁም ቁርጠኝነት ያሳየ ነበር ብሏል መግለጫው።

መላው የሀገራችን ሕዝብ በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንግዶችን በክብር ከመቀበል ጀምሮ በየሆቴሎቹ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ በማድረግ፣ የሚያልፉባቸው መንገዶች ሲዘጉ በትዕግስት ቅድሚያ ሰጥቶ በማሳለፍ, ከፀጥታ ኃይሉ የሚሰጠውን መመሪያ በቅንነት በመቀበል ትብብራቸውንና አጋርነታቸውን በማሳየታቸው, የፀጥታና ደህንነት አመራሮችና አባላትም በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣታቸው ጉባኤው ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላምና በስኬት በመጠናቀቁ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡