የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የዳያሥፖራ አባላት፣ የኮሚዩኒቲ አመራሮችና የተለያዩ አደረጃጀቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
በዳያስፖራው የተፈጠረውን መነሳሳትና የአንድነት ስሜት ቀጣይነት ባለው መልኩ በሀገር ልማትና ዕድገት ለማሳተፍ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት የዳያስፖራ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በዕውቀት ሽግግር፣ ወደ ሃገር በሚላክ የውጭ ምንዛሪና በሌሎች ወሳኝ የሀገር ልማት ጉዳዮች ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከርና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ ኤጀንሲው ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በኤጀንሲው የሥራ ሃላፊዎች ቀርቧል።
ኤጀንሲው ዳያስፖራው በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ያለምንም የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ለማገልገል የሚያስችል ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በማካሄድ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
ዳያስፖራው በትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች አሻራውን በማኖር ረገድ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡
ኤጀንሲው ዳያስፖራው በሀገራዊ ልማት በበለጠ እንዳይሳተፍ ማነቆ የሆኑት፣ በየደረጃው ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት፣ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት አለመስራት፣ የተጠና ፕሮጀክት አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ በቂ ገንዘብ ሳይዙ መሬት የማግኘት ፍላጎት እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ይልቅ ወደ አገልግሎት ዘርፍ የማዘንበል ችግሮች መኖራቸውንም አመላክቷል።
ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ በያገባኛል መንፈስ እንዲሳተፍ ሃገራዊ የዳያስፖራ ምክር ቤት ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።
አሁን ላይም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት የተለያዩ አደረጃጀቶች ህብረት ለመመስረት ከማህበራት የተውጣጡ አደራጅ ኮሚቴ ለሟቋቋም መስማማታቸውን እና ህብረቱን ለመመስረት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በሀገራዊ ዳያስፖራ ምክር ቤት የሚወክሏቸውን አመራር በመምረጥ ተሳትፏቸውን እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።