የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ለገበታ ለሀገር 27 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ

 

ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት አብሮነታቸውን ለማሳየት ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት 27 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል በቀጣይ ሳምንት በሚዘጋጀው የእራት መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ እጣ የወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ዝርዝርም ይፋ ሆኗል።

በብሔራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የውጭ ድጋፍ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ለሚገነቡት ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነው።

“ለኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ዳያስፖራው ድጋፉንና አብሮነቱን እያሳየ ነው” ብለዋል።

በዚህ አመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመላው አለም ከሚገኘው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት 50 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አብራርተዋል።

በሁለተኛው ሩብ አመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 15 ሚሊዮን ብር 27 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ድጋፉን ኢትዮጵያ ውስጥ በተከፈተው አካውንት፣ በሚሲዮኖችና ዳያስፖራው በግል፣ በቡድን፣ በማህበርና በድርጅት ስም ለፕሮጀክቱ ገቢ አድርጓል።

በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ልማት ለመሳተፍ እያሳዩ ያለውን ተነሳሽነት በመጠቀም በቀሪው ጊዜ ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደው የገበታ ለአገር የእራት መርሃ ግብር ላይ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ከአፍሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅና ከሌሎች አካከባቢዎች እጣ የወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለተለያዩ ሰብአዊ እርዳታና ኢትዮጵያን ለማልማት መንግስት በሚቀርጻቸው ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው በእውቀት፣ በገንዘብና በሌሎች ተነሳሽነቱ መጨመሩን ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ ድጋፍ ለቤተሰብ፣ ለልጅና ለአገር ቋሚ ቅርስ ጥሎ የሚያቆይ በመሆኑ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አምባሳደር ብርቱካን አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ የሆኑትን ኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች ስራ ለማስጀመር የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ እንደሆነ ይታወቃል።