የጠነከረችና የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አቅደው እየሰሩ መሆናቸው ተገለጸ

ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) በቀጣናው የሚስተዋለውን ችግር ቀርፈው የጠነከረችና የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በውጥን እየሰሩ መሆናቸው ተገለጸ።

የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ከውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር በአፍሪካ ቀንድና በቀጣናዊ ደህንነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ትብብርን ማጠናከር ለቀጣናው ውህደት መሠረት የሚጥል መሆኑ በተደጋጋሚ እንደሚነሳና ይህንንም የሚያጠናክር ስራዎች በስፋት መስራት እንደሚጠበቅ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ውይይቱ “ለውስብስብ ጉዳዮች አማራጭ መንገዶችን በመፈለግ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ደህንነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሔደ ሲሆን ይህን ውጥን እውን ለማድረግ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚኖሩ ሀገራት መተባበርና የጋራ አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ ያላቸው ያልጠነከረ ግንኙነት፣ ሰላም እጦት፣ መፈናቀልና ጦርነት ለዘመናት ችግር ሆነውባቸው መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን ይህንን በቀጣናው የሚስተዋለውን ችግር ቀርፎ የጠነከረች የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በውጥን እየሰሩ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

ለዚህም በቀጣናው ያሉ እድሎችንና ፈተናዎችን በመለየት ዘላቂና አስተማማኝ ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር የቀጣናውን አገራት ትብብር የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል ውይይትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 2023 በጅቡቲ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ትብብሩንም ለማጠናከር የቀጣናው ተወካዮች ሁለተኛ መድረክ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አካሂደዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የሚያጋጥሙ ወቅታዊ ፈተናዎችን ለመሻገር መሰል ውይይቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋና የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ በቀጣናው የደህንነት ምህዳር ላይ እየታዩ ያሉ ለውጦችና አንድምታቸው፣ የውጭ ኃይሎች በቀጣናው ደህንነት ላይ ያላቸው ሚና ላይ ያተኮሩ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይቶች ተካሂዶባቸዋል።