የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ሰላምና ልማት የሚያፋጥን የ5 ዓመት መርሃግብር ይፋ ሆነ

የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች የሰላምና ልማት ግንባታ በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን የሚሰፍን የአምስት ዓመታት ሁለትዮሽ መርሃግብር ይፋ ሆኗል፡፡

መርኃግብሩ በሁለቱ ክልሎች የጋራ ልማት ላይ ያተኮረ እና ህዝብ ለህዝብ በማገናኘት በየጊዜው የጋራ መድረኮችን በማከናወን መሰረታዊ የግጭት አፈታት ዘዴን ያቀፈ ነው ተብሏል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኢፌደሪ ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ሁለቱ ክልሎች ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፎረምን በማጠናከር ለአምስት አመታት የሚቆይ የጋራ መርሃግብር ነድፈው መስራታቸው ልማት በማፋጠንና የጋራ የገበያ ስርዓትን በመተግበር በፋይናንሱ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ይችላሉ ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ሀገሪቱ እስካሁን በነበራት ጉዞ ከፍተኛ የትግልና አብሮነት ታሪክ ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፣ የበለጸገች እና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በክልሎቹ መካከል የተጀመረው የአምስት አመታት ዕቅድ መርሃግብር ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌፊ መሐመድ ኡመር በበኩላቸው፣ መርሃግብሩ የሚተገበረው በሁለቱ ክልሎች ወሰን አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የሁለቱን ክልሎች ሁለንተናዊ ትስስራቸውን በማጠናከር ሰላምና ልማትን በዘላቂነት ለማስቀጠል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ክልሎቹ በሀገሪቱ ከፍተኛ ሽፋን የሚይዙ በመሆናቸው የሁለቱ ክልሎች ሰላም የሀገሪቱ ሰላም ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

(በብርሃኑ አበራ)