የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ አዲስ አበባ ገቡ

የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ

ሰኔ 01/2013 (ዋልታ) – የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።

ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ አዲስ አበባ የገቡት ለአንድ ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በቦሌ ዓላም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ  የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

የኬኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪይቸል ኦማሞ ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያና የኬኒያ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1954 የኢትዮጵያ ቆንስላ በኬኒያ ተከፍቶ ነበር የተጀመረው።

በመቀጠልም ኢትዮጵያ በ1961 የመጀመሪያውን አምባሳደር ወደ ኬኒያ የላከች ሲሆን፣ ኬኒያ ደግሞ በ1967 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች።

ሁለቱ አገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ያቋቋሙ ሲሆን፣ የጋራ የድንበር አስተዳደር ኮሚሽን አቋቁመው በርካታ ውይይቶች ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሁለቱ አገራት መሪዎችም የሁለዮችሽ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር ተደጋጋሚ ጉብኝትና ውይይቶች ሲያደርጉ እንደቆዩም ይታወቃል።