የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙርያ ሳምታዊ መግለጫ ሰጠ

መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙርያ ሳምታዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንቱ በፓለቲካው እና ዲፕሎማሲ ረገድ በዚህ ሳምንት ከአሜሪካ ጋር ውይይቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ምንም እንኳን ከ85 በመቶ በላይ የአባይ ውሀ ባለቤት ኢትዮዽያ ብትሆንም ህዝቦቿ በጨለማ ውስጥ እንደሚኖሩና ይህን እውነት ለመቀየር ከውሀው ተጠቃሚነት ህጋዊ መብት እንዳላት ለሀገራቱ መብራራቱን አንስተዋል::
ኢትዮዽያም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ፍትሀዊ ክፍፍል እንዲኖር የምትሻ ሀገር መሆኗን ገልፀዋል::
በተጨማሪም በውጭ ያሉ ኢትዮዽያውያን የአለም አቀፉ ማህበረሰብ መሬት ላይ ስላለው እውነት እንዲያውቀው የተዛቡ ትርክቶችን በመመከት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አበረታች በመሆኑ በትኩረት መሰራት ያለበት ጉዳይ ስለመሆኑ ተናግረዋል::
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም የኳታር ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ተሰማርተው የኢትዮዽያን የኢንቬስትመንት ጎዳና እንዲቀላቀሉ ጥሪ መቅረቡን አውስተዋል::
በሱዳንና በኢትዮዽያ መካከል ያለውን ቅራኔ ለመፍታትም ኢትዮዽያ አሁንም ቢሆን በድርድር የመፍታት ፍላጎት እንዳላት አምባሳደሩ ገልፀዋል::
በኢትዮዽያና በሱዳን መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በርካታ ሀገራት የማሸማገል ፍላጎታቸውን ቢያሳዩም ኢትዮዽያ ግን የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንድማትቀበል አስታውቀዋል::
የኢትዮዽያ እና የኤርትራን ግንኙነት በተመለከተም ምንም እንኳን ሁለቱ ሀገራት ቀደም ሲል የነበራቸው ግንኙነት ሻካራ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደተሻለ መንገድ ለማስቀጠል እየሰራች ነው ብለዋል::
(በሄብሮን ዋልታው)