የዜጎች የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ

መስከረም 13/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በ46 ተቋማት ውስጥ 226 የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች ለምተው ከ2 ሚሊዮን በላይ ተገልጋዮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ከ121 ወረዳዎች ለተውጣጡ 250 ወጣቶች በኢትዮጵያ በተዘረጉ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎትና አገልግሎቱን መጠቀም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱ ተገልጿል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ አይ ሲ ቲ ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ሲናሞ (ዶ/ር ኢንጂ.) ወጣቶቹ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት አምባሳደር በመሆን ለተደራሽነቱ መስፋት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚያንቀሳቅሱ ናቸው ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ ወጣቶች እነዚህን አገልግሎቶች በመጠቀምና ሌሎችን በማስጠቀም ገቢ ማግኘት ይቻላሉ ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ ወጣቶቹ በየወረዳው በሚገኙ የወጣት ማዕከላት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶችን ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲያደርጉ እና አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚገባቸው ተገልጿል።
በመድረኩ ስለ ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶቹ በአልሚ ድርጅቱ ማናጀር በአቶ እውነቱ አበራ በኩል ገለፃ የቀረበ ሲሆን ተግባራዊ የአጠቃቀም ስልጠናም ተሰጥቷል።
በስልጠናው የተሳተፉ ወጣቶችም መድረኩ ሰፊ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው የገለፁ ሲሆን በየአካባቢያቸውም የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች አምባሳደሮች ሆነው ለማገልገል ቃል መግባታቸውን ከኢኖቬኝንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።