የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት ቅመማ እና አገልግሎት መስጫ ተቋም ተመረቀ

 

ጥቅምት 17/2016 (አዲስ ዋልታ) የየም ብሔረሰብ ባህላዊ መድኃኒት (ሳሞ ኤታ) ቅመማ እና አገልግሎት መስጫ ተቋም ተመረቀ።

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል ብሔረሰቡ ጠብቆ ያቆየውን ባሕላዊ መድኃኒት ለቀማ እና ቅመማ ሂደትን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዋቻሞ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች በባሕላዊ መድኃኒት ለቀማ እና ቅመማ ሂደት ዙሪያ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በተቋሙ ምርቃት ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን በቦር ተራራ በዓመት አንድ ቀን ጥቅምት 17 ለአካባቢው ማህበረሰብ እና ለእንስሳት ባህላዊ ህክምና የሚሆን የዕፅዋት መድኃኒት ይለቀማል።

ማህበረሰቡ ቀኑን ጠብቀው የማለዳ ፀሐይ ቀድመው ወደ ቦር ተራራ በመውጣት የሚበቅሉ ዕፅዋቶችን የምለቅሙ ሲሆን የተለቀሙት ዕፅዋቶች በማህበረሰቡ ፈውስን የሚያጎናፅፉ ፍቱን መሆናቸው ይታመናል።

ከጅማ፣ ከጌዴኦ፣ ከሰቃ፣ ከቀርሳ ወረዳ የመጡ የየትንኛውም ሃይማኖት ተከታይ የባሕል መድኃኒት አዋቂዎች ተራራው ላይ ይወጡና ለአንድ ዓመት የሚሆናቸውን የዕፅዋት መድኃኒት ቀኑን ሙሉ ይለቅማሉ፤ ተግባሩም ‘ሳሞኤታ’ (በየም ባህል የከረመ መድኃኒት ለቀማ) ተብሎ ይጠራል።