የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶንያ የ100 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ካርታ አስረከበ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በድሬዳዋ ከተማ የ100 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ካርታ አስረከበ።

ከተማ አስተዳደሩ በአዲስ አበባ የሜቄዶንያ መርጃ ማዕከል በመገኘት ድጋፉን ያበረከተ ሲሆን፣ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የሜቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሀገር ባለውለታ ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ ዘር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይገድበው በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በመገኘት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አስተዳደሩ ያበረከተው የመሬት ካርታ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ በቀጣይም የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ እንዲሁም ለማዕከሉ የንፅህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ህዝቅያስ ታፈሰ በበኩላቸው፣ መቄዶንያን በድሬ ቲቪ እንዲሁም በድሬ ኤፍ ኤም ነፃ የአየር ሰዓት ሰጥተን የሚሰራውን በጎ አላማ ለህዝብ እናስተዋውቃለን ብለዋል።

የመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ቢንያም በለጠ የማዕከሉን አላማ ተረድተው ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፤ ለውለታችሁ ፈጣሪ ዋጋችሁን ይክፈላችሁ ብለዋል።

የተቸገሩትን መርዳት ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ሌሎችም ተቋማት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን መልካም አርአያነት እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን እንደሚያስተናግድ ገልጸው፣ ተጨማሪ 6 ሺህ ሰዎችን ለመቀበል ያቀደውን ግብ እውን ለማድረግ በቅርቡ 300 ጎዳና ላይ የወደቁ ሰዎችን ያነሳል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ማእከሉ የሚያስገነባውን የህንጻ ግንባታ ለማጠናቀቅ በቀጣይ የሁሉም ድጋፍና እገዛ እንዲታከልበት መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።