የጎንደርና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የስራ ስምምነት ተፈራረሙ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር አስራት አፀደወይንና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ታፈረ መላኩ ናቸው የእህትማማችነት የስራ ስምምነቱን የተፈራረሙት።

የስራ ስምምነቱ በመምህራን ልማት፣ በቤተ ሙከራ ስራዎች፣ በጥናትና ምርምር ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈች ጥናትና ምርምር በማድረግ ማህበረስቡን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በዝግጅቱ ላይ “የዩኒቨርስቲዎቻችን አሁናዊ ተግዳሮቶች” የሚል መፅሐፍ ተመርቋል።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ የተፃፈው መፅሐፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ችግሮችን ያሳየ ነው ተብሏል፡፡

በመፅሃፉ የተማሪዎች ምገባ ላይ ያለው ማነቆ እንደ ትምህርት ተቋምና እንደ ሃገር ያሳደረውን ተፅእኖ በግልፅ ያስቀመጠ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሃገሪቱ የሚታዩ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች ምክንያት በተማሪዎች፣ በትምህርት ማህበረሠቡ እና በተቋማቱ ኃላፊዎች ላይ የሚደርሱ ጫናዎች በግልጽ ያስቀመጠ የመፍቻ መንገዱንም ያመላከተ እንደሆነ ተነስቷል።

በ260 ገፅ፣ በ4 ምዕራፎች በ20 ንኡስ ምዕራፎች የተቀነበበ መፅሃፉ በይዘቱ፣ በአፀጻፋና ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ በምሁራን ዳሰሳ ተካሂዶበታል።

(በምንይሉ ደስይበለው)