የጥምቀት በዓልን ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ

          የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ

በዘንድሮው ዓመት የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ካለፈው ዓመት በተለየ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ በበዓሉ ወቅት የሚገኘው ታዳሚ መርኃግብሩን እንዲከታተል ቦታ ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በሚከበርበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የጤና ሚኒስቴር ያወጣቸውን መመሪያዎች ለመተግበር እንዲያስችል ኮሚቴ መዋቀሩን የገለፁት ምክትል ከንቲባው፣ የታዳሚው ደህንነት እንዲረጋገጥ በፀጥታ ሁኔታው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በሚያርፉበት አካባቢ የጥንቃቄ ስራ በመስራት ከበዓሉ ጎን ለጎን ታዳሚው ራሱን በመጠበቅ በዓሉን እንዲያከብር ዝግጅት ከመደረጉ በተጨማሪ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ተሾመ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ የኃይማኖት ክብረ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ሲሆን፣ በበዓል አከባበሩ ውስጥ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ይተዋወቁበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ በዓሉን በምታከብርበት ወቅት ከሀገር ውስጥ እና ከአለም አቀፍ ጎብኝዎች የምታገኘው ገቢ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ መመዝገቡ የሚታወስ ነው፡፡

(በሱራፌል መንግስቴ)