የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ 2ኛው “የመደመር” መጽሐፍ ነገ አንባቢያን እጅ ይደርሳል

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተዘጋጀው እና “የመደመር መንገድ” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ነገ ለአንባቢያን እንደሚደርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡

መጽሐፉ የለውጡን ፈለግ እና መደመር ያለፈበትን መንገድ ወደ ኋላና ወደ ፊት መለስ ቀለስ እያለ ይዳስሳል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

በብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰውን ለውጥ የወለዱ አስተሳሰቦች ምን እንደሆኑ፣ የሪፎርም ጉዞው ከጥንስሱ ጀምሮ ምን እንደሚመስል፣ በሂደት የተፈጠሩ መልካምና ፈታኝ አጋጣሚዎች እንዲሁም ተጓዳኝ ታሪኮችን መያዙንም ነው ዶ/ር ዐቢይ የገለፁት፡፡

“ከዛሬ ነገ እጽፋቸዋለሁ እያልኩ ሳልጽፋቸው በልቤ ሰንዱቅ እንደታሸጉ ለረጅም ዘመናት አብረውኝ የቆዩ ትዝታዎቼ እና ከጓዶቼ ጋር የተጋራኋቸው ወዳጃዊ ሐሳቦች ጭምር ተካትተውበታል” ብለዋል፡፡

መጽሐፉ በብዙ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንደሚሰጥም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ለወጣው መጽሐፍ እንደ ተከታይና አስረጂ ሆኖ እንዲያገለግል ዘርዘርና ሰፋ ብሎ፣ ከመጠነኛ የአጻጻፍ ቅርጽ ለውጥ ጋር የተሰናዳ መጽሐፍ መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

መጽሐፉን ለማዘጋጀት ሁለት ዓመታትና ከዚያ በላይ የሆነ ጊዜ መፍጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

መጽሐፉ በሁለት ቋንቋዎች በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ተሰናድቶ የኅትመት ሥራው በመጠናቀቁ ነገ አንባቢ እጅ ይደርሳል ተብሏል።