የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተገነቡ 105 ፕሮጀክቶች ተመረቁ  

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት እየተገነቡ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል 105ቱ ተመረቁ።

በአጠቃላይ በልዩ ዞኑ እየተሰሩ ካሉ 125 ፕሮጀክቶች መካከል 105ቱ በዛሬው እለት የተመረቁ ሲሆን፣ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ትምህርት ለአንድ ሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ በዛሬው እለት የተመረቁትን ትምህርት ቤቶች በመንከባከብ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል በሰበታ አዋስ ወረዳ የሚገኘው የኢፋ ቦሩ አዋሽ መልካ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኝበታል።

ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ስድስት ወራት የፈጀ ሲሆን፣ 34 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታልም ነው የተባለው።

(በሱራፌል መንግስቴ)