የ2013/14 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ ነው – የግብርና ሚኒስቴር

የካቲት 25/2013 (ዋልታ) – የ2013/14 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋ፣ በዘንድሮው የምርት ዘመን 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈፀም እና ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት በማቀድ ሙሉ በሙሉ ግዢ መፈፀሙን ገልጸው፣ ግዢ ከተፈፀመው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ጅቡቲ ወደብ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሃገር ውስጥ ማጓጓዝ ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ጅቡቲ ወደብ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 98 በመቶ የሚሆነውን ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።

አጠቃላይ እንደ ሃገር ከታቀደው 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 31 በመቶ የሚሆነውን ማጓጓዝ ተችሏልም ነው ያሉት።

ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ወደ ህብረት ስራ ማህበራት የተጓጓዘ ሲሆን፣ አሁን ካለው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ወደ ህብረት ስራ ማህበራት የተሰራጨ መሆኑንም ገልፀዋል።

ወደ ተጠቃሚው አርሶ አደርም 656 ሺህ 768 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የተሰራጨ ሲሆን፣ ወደ ህብረት ስራ ማህበራት ከተጓጓዘው ውስጥ 16 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነውን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንደተቻለ የገለፁት አቶ መንግስቱ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርስ ይደረጋል ብለዋል።

የዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የ3 ነኝብ 1 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው የተጠቀሰ ሲሆን፣ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት መንግስት 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ድጎማ በማድረግ የአፈር ማዳበሪያ ግዠ መፈጸሙ ነው የተገለጸው፡፡

እስካሁን በአፈር ማዳበሪያ ግዢና የማጓጓዝ ስራ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመለየት እንዲሁም ውጤታማ ስራ የሰሩና ትልቅ ሚና የተጫወቱ ባለድርሻ አካላትን የማመስገንና እውቅና የመስጠት ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ካለፉት አመታት የተሻለ ስራ መስራት መቻሉን እና በያዝነው የምርት ዘመን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ቀድሞ በማጠናቀቅ የአፈር ማዳበሪያው በወቅቱ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ የሚያስችል ስራ መሰራቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።