ድህነት ያንገሸገሸው የስንዴ ልማት ዘመቻ በኢትዮጵያ

በሠራዊት ሸሎ

ድህነት አንገት ያስደፋል ያዋርዳማል የራስ መተማመንን እያጎሳቆለ ልመናና ተመፅዋችነትን ያስከትላል። ላለዉ መገዛትንና የራስ ማንነትን ለሌላ መስጠትን አስከትሎ ነፃነት ማጣትንና ፍርሃትን ያነግሣል።

እኩልነት ጠፍቶ ያለው የሌለውን የሚገዛው ለሀሳቡም ተገዢ የሚያደርገው ድህነት የተጠናወተውን ግለሰብ ወይም አገርን ነው። ብቻ ድህነት የአሳቤ ጉድልነትና ዕውቀት ማነስ ምልክት ቁርጠኛ በሆነ ስሜት የራስ ዕውቀትን አስተባብሮ ተፈጥሮን ለሰዎች ጥቅም የማዋል ትጋትን የሚያኮስሰ ጥረት ያለማድረግ ምክንያት ነው።

አርቆ በማሰብ ባለሙት ዓለማና መንገድ  ላይ ትኩረት በማድረግ  ለተግባራዊነቱ ስኬት ተግቶ የሠሩት በዓለም ላይ ልዩነት አምጥቷል። ለልዩነት መፈጠር ምክንያቱ ደግሞ ነባራዊ ሁኔታን በመገንዘብና ችግርን በጥልቀት በመረዳት ለችግሩ ፈጣን መፍትሔ በማበጀት ለመፍትሔው ገቢራዊ መሆን ቁርጠኛ አቋም ይዞ መገኘት ነው።

የድህነት ምንጩ የእሳቤ ልዪነት የወለደው አለመሥራት እንጂ ተፈጥሮ ለሁሉም ሰብአዊ ፍጥረት እኩል ዕድል ሰጥታለች። ላለመበልፀግና ላለመሰልጠን ምንጩ  ግን የእይታ ችግርና የሐሳብ ድህነት የወለደው ይቻላልን ተቀብሎ አለመነሣት ሊሆን ይችላል።

ከኢትዮጵያ እኩል ደረጃ የነበሩ አገራት  በአርባና ሀምሳ ዓመታት ውስጥ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ችሏል።

ለዚሁ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት አራቱ የእስያ አገራት (Asian tigers) ናቸው ። ሲንጋፖር ሆንኮንግ ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ። እነዚህ አገራት ኋላ ቀር የነበሩና በ1960ዎቹ ከድህነት ለመላቀቅና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት በማሰብ በአገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመሥርተው ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና የወጭ ንግድ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ በመቅረጽና በመተግበር ለውጥ ያስመዘገቡ አገራት መሆናቸው ይነገራል።

ለዚህ ፈጣን ለውጥ የማምጣታቸው  ምክንያት ደግሞ ለገቢራዊነቱ የዜጎቻቸው ተነሣሽነትና የአገራቱ መሪዎች የሰጡት ቁርጠኛ አመራር መሆኑ ይወሳል።

እነዚህ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ጋር እኩል ደረጃ የነበሩ አገራት ወደ ዕድገት ማማ ሲገሰግሱ ኢትዮጵያ ግን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በድህነት ቀንበር ስትማቅቅ ባለችበት ቆይታለች።

የስንዴ ብዝኅ-ሕይወት መገኛ የሆነችው አገር በስንዴ ምርት ራሷን ባለመቻሏ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በየዓመቱ ስንዴ ታስገባለች። ድርቅ ሲገጥማት ደግሞ በልመናና በግዢ ዜጎቿን እንደምትመግብ መረጃዎች ያስረዳሉ።

አምራች የሰው ሃይል፣ሰፊ መሬት፣ ከራሷ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ የከርስና የገፀ ምድር ውሃ ባለቤት ሆና ሳለች ግን መለያዋና ስሟ በድህነት ይወሣል።

ታዲያ ኢትዮጵያ ለምን ደሃ ሆነች?  ጀግንነቷ በዓለም የተነገረላት አገር ለምን እህል ለመነች? በተፈጥሮ ፀጋ የታደለችና ከርሷ አልፎ ለሌላ የሚተርፍ ሀብት እያላት ለምን መበልፀግ አቃታት? መልሱ ከእያንደንዱ ዜጎቿና ከሚመሯት መሪዎቿ  ቁጭትና የለውጥ  ተነሣሽነት ይወሰናል።

ለዘህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ደ/ር)” ኢትዮጵያ እንዴት ደሃ ትሆናለች? እንዴትስ ስንዴ ትለምናለች ይኼ ሊያስቆጨን ይገባል፣ ከእንግዲህ ወዲያ ኢትዮጵያ ስንዴን አታስገባም የሚለው ራዕይ ለብዙዎች በቀላሉ የሚቀበሉትና የሚዋጥላቸው አልነበረም፡፡ ከጅምሩ እናስባለን ያህንኑ እንናገራለን ለዚያም ተግተን እንሠራለን፣ አሳክተን እኛም ዓለምም በጋራ ማየት እንድንችል እናደርጋለን ” ያሉት ።

ከዚህም ቁጭት ከወለደው ተነሣሽነት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለዘመናት በበሬ ጫንቃ ላይ ከተመሠረተው ኋላ ቀር አስተራረስ ለመላቀቅ ገና ግብግብ የጀመረችው።

በዚህም ላለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና  ለውጥ ለማምጣት የተያዘው ስትራቴጂ  መልካም ጅምር እየታየበት ይገኛል።

በተበጣጠሰ ማሣ በበሬ ሲያርሱ የነበሩ አርሶ አደሮች  በኩታገጠም እርሻ በትራክተር ማረስ ጀምረዋል። በመኸር እርሻ ላይ ብቻ ታንቆ የኖረው የስንዴ እርሻ በበጋ መስኖ ማምረት እንዲሁም በእርዳታ እንጂ አምርቶ የማያውቁ አርብቶ አደሮች እንኳን ስንዴን ማምረት ጀምሯል።

በእርሻ ስራ የማይታወቁና በረሃ ተደርጎ ለዘመናት የቆዩ ሰፋፊ መሬቶችም ለእርሻ እየዋሉ ነው፡፡ በዚህም የስንዴ እርሻ ያልተለመደባቸው ቆላማ የአገሪቱ ክፍሎች  ስንዴን በሰፊው ማምረት ችለዋል። ለአገር ልማት ያልዋሉና በከንቱ ይፈሱ የነበሩ የዉሃ ጅረቶች  የልማት አጋር ሆነው በበረሃ ውሰጥ የስንዴ ሰብል ተንዠርግጎ ማየት አሁን ኢትዮጵያ የታደለችውን ፀጋ ለመጠቀም አይኗ መከፈቱን ያበስራል፡፡

ግብርናን ወደ ሙሉ ሜካናይዝድ እርሻ የመቀየር ውጥን በሶማሌና በአፋር ክልሎች ተረጋግጧል። አርሶ አደሩ ዝናብ ጠብቆ ከማምረት ልምድ የማላቀቅና መሬት ወሃና አምራች የሰው ሃይል አቀናጅቶ የመጠቀም ውሉ አሁን የተሣካ ይመስላል።

ይህ ቁጭት የወለደውና በስንዴ ልማት የተስተዋለው  ቁርጠኝነት  ኢትዮጵያ ከስንዴ ተመጽዋችነት እንድትላቀቅና ወደ ውጭ ገበያ አቅራቢነት እያሸጋገራት ነው፡፡

ከለውጥ ማግስት ጀምሮ  ኢትዮጵያ የስንዴን ሰብል በመኸር ዝናብና በበጋ መስኖ  በማምረት የውስጥ ፍላጎት ለማሟላትና የተረፈውን ወደ ውጭ ለመሸጥ አጀንዳ አድርጋ መነሳቷና ለተግባራዊነቱ ትኩረት ሰጥታ መሥራቷ ለስኬቷ መንገድ ሆኖላታል።

በተለይ የለውጡ መንግሥት በ2011 ዓ.ም ሀገራዊ የስንዴ ምርት ማሳደጊያ ፕሮግራም መንደፉና ለውጤታማነቱ የተሰጠው የተቀናጀ አመራር ለስንዴ ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ያመለክታል።

በዚሁ  በ2011ዓ.ም በመኸር ወቅት ከሚመረተው በተጨማሪ ስንዴን በበጋ ወቅት የማምረት ሥራን ለማከናወን አዋሽ ሸበሌ ኦሞና ፈንታሌ የመስኖ አውታሮችን ለሥራ በማዋል 3ሺህ 502 ሄክታር መሬት በማምረት አምስት መቶ ሺህ ኩንታል በማምረት የተጀመረው የስንዴ እርሻ አሁን እየተገኘ ላለው የስንዴ ልማት ውጤት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ይህንን ተሞክሮ ወደ ሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በማስፋት በ2012 ዓ.ም 20ሺህ ሄክታር በማልማት 700 ሺህ ኩንታል፣ በ2013 ዓ.ም 1መቶ 17ሺህ ሄክታር በማልማት 3 ነጥብ ስድስት ሚልዮን ኩንታል፣ በ2014 ዓ.ም ደግሞ በመስኖና በልግ ልማት 6መቶ72ሺህ ሄክታር በማልማት 24 ነጥብ 5 ሚልዮን ምርት ማምረት ተችሏል።

በ2014/15 የምርት ዘመን ደግሞ በመኸር ወቅት 2ነጥብ ስምንት ሚልዮን ሄክታር በማልማት 1መቶ12 ሚልዮን ኩንታል ምርት ማምረት የተቻለ ሲሆን በዚሁ የምርት ዘመን በመኸርና በመስኖ ስንዴን በስፋት በማምረት የሀገር ፍጆታን ከሟሟላት ባሻገር ወደ ውጭ ለመላክ ዕቅድ ተይዞ የተገባበትና ታሪካዊ ለውጥ ማስመዝገብ እንደተቻለ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በስንዴ ምርት በተገኘው ስኬትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ካቆመች ሁለት ዓመት ሆኗታል። ይህ በአጭር ጊዜ የተገኘው ውጤት የአመራር ቁርጠኝነትና የባለድርሻ ቅንጅታዊ አሠራር መጎልበት መሆኑን ያሳያል ።

ይህ ስንዴን በመኸርና በበጋ መስኖ በስፋት ማምረት እንደሚቻል በአመራሩ የተወሰደው ቁርጠኝነትና ቁጭት ብሎም  የምርምር ተቋማትና የዘርፉ ባለሙያዎች  ድጋፍና ተነሳሽነት የጎላ መሆኑንም ያመላክታል ።

በአጠቃላይ በለውጡ ዓመታት በስንዴ ልማት የተመዘገበው  ውጤት የአመራሩን፣ የምርምር ተቋማትና የአምራቹን ቁጭትና ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ለዚህ ሁሉ ስኬት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያሳዩት ቁርጠኛ አመራር ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ  ለትውልድ ደግሞ አገር ወዳድነትንና ቁርጥኝነትን የሚያስተምር ህያው መልዕክት ነው፡፡

ቆላ ደጋንና ወይናደጋን ሳይለይ ይህ የተጀመረው ስንዴን በስፋት የማምረት ሂደት አሁን አየታየ ባለው ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ሰፋፊ መሬትና ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችን ምርታማ በማድረግ በአራቱም አቅጣጫ ባሉ የኢትዮጵያ ሰፋፊ የእርሻ ማሣዎች የስንዴ ዘለላ ተንዠርግጎ የሚታይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ።

በድርቅና በምርት አቅርቦት እጥረት ምክንያት ከውጭ የሚገባው ስንዴን ታሪክ ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞን ለማፍጠንና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ዓለማት ምርቷን ለመሸጥ ያለመችውን ህልም ለማሳካት  የአመራሩ የግብርና ባለሙያውና  የተመራማሪው እንዲሁም የአርሶና አርብቶ አደሩ ሚና ተተኪ የሌለው በመሆኑ ሁሉም  የድርሻውን መወጣት ታሪካዊ ሃላፊነት መሆኑን ልብ ይለዋል።

የስንዴ ተመፅዋችነት ቀርቶ የድህነት አረንቋ ታሪክ ተደፍኖ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ያነገበውን ስንዴን የጫነው ፉርጎ እኛን ለረዱት ውለታውን ለመመለስ ምርቱን  ከአገር  ማዶ ሲያራገፍ ማየት የሁሉም ዜጋ ራዕይ ሊሆን ይገባል እንላለን !!

ቸር እንሰንብት!!