ግብጽ ጨዋማ ውሃን አጣርታ እንድትጠቀም ቻይና ምክረ ሐሳብ አቀረበች

ሰኔ 02/2013 (ዋልታ) – ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጫና ለመፍጠር በማለም ለቻይና ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ በመሆኑ ጨዋማ ውሃን አጣርቶ የመጠቀምና መሰል አማራጮችን እንድትጠቀም ቻይና ምክረ ሐሳብ አቀረበች፡፡
ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ለማድረግ ያልዞሩበት የዓለም አገራት የሉም ማለት ይቻላል፤ ይሁን እንጂ ሁለቱ ሃገራት ያደረጉት ጥረት ምንም ፍሬ ሊያፈራላቸው አልቻለም፡፡
ግብጽም በቅርቡ የመጨረሻዋ የሆነውን የአሸማግይን ጥያቄ ለቻይና አቅርባ ጥያቄዋ ተቀባይት በማጣቱ የአቋም ለውጥ ማሳየቷን አል ሞኒተር ኢጂፕት አስነብቧል፡፡
የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ ሃገራት መካከል በቀዳሚዎቹ ተርታ የምትቀመጠው ቻይና ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንደማታደርግ ለግብጽ እንቅጩን እንደነገረቻትም አል ሞኒተር ጠቁሟል፡፡
ባይሆን ጨዋማ ውሃሽን በማጣራት የውሃ ሃብቶችሽን በመጠበቅ እንዲሁም በውሃ ቆጣቢ እርሻ አተገባበር ላይ የራሴን ተሞክሮ በማካፈል ልተባበርሽ እችላለሁ ብላታለች ለግብጽ፡፡
አማራጭ ያጣችው ግብጽም የአቋም ለውጥ በማድረግ በቻይና በኩል የቀረበላትን ጨዋማ ውሃዋን አጣርቶ የመጠቀምና መሰል አማራጮች ተቀብላ ለመስራት መስማማቷ ተገልጿል፡፡