ጎረቤት ሀገሮች ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለው የአረንጓዴ አሻራ በጋራ የመልማት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – የተለያዩ የጎረቤት አገሮች ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለው የአረንጓዴ አሻራ በጋራ የመልማት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ከሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለማልማት እቅድ የያዘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን የሚሆኑ ችግኞች ለጎረቤት አገሮች እንደሆነ ይታወቃል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለው አረንጓዴ አሻራ በአሁኑ ወቅት በተለይ ጂቡቲና ደቡብ ሱዳን በጋራ የመልማት ፍላጎት አላቸው።

በአገሪቱ እየተዘጋጀ ያለውን ችግኝ በመውሰድ ለመትከል በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከሚገኙ ሌሎች አገሮች ጋርም ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

“ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ብቻዋን የምታደርገው የችግኝ ተከላ በቂ አይደለም ብላ ታምናለች” ያሉት አቶ ሳኒ፤ በበጀት ዓመቱ አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለጎረቤት አገሮች ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት ጥያቄ ያቀረበችው በጋራ የመልማት ሃሳብን ለማጋራት መሆኑንም ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

እስከተያዘው በጀት አመት መጨረሻ 14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ እንደምትተክል እና ቀሪውን በቀጣዩ ዓመት ተክላ እቅዷን እንደምታሳካም ተጠቁሟል።