ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የ40ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 30/ 2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የ40ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱን የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ተስፋዬ ዳባና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበራ ፀጋዬ ተፈራርመዋል፡፡
ድጋፉ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለሚሰጣቸውና ወደፊትም ለሚያካትታቸው አዳዲስ ካሪክለሞች የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ክለሳ ለማድረግ የሚያስችለውን ስራ ለመደገፍ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለፁት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርአት ከማሻሻል አንፃር በፌዴራል ፖሊስ፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፣ በፍርድ ቤቶችና በፀጥታ ሃይሎች በኩል ትላልቅ ማሻሻዎች እየተደረጉ ነው፡፡
አሁን የሚደረገዉ ድጋፍም በተለይም በፖሊስ በኩል ያለዉ ስራ በእዉቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማስቻሉም በተጨማሪ የምርመራ ሂደቶች ከዘልማዳዊ አሰራር ወጥተው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ ለማስቻል ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረዉ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር አበራ ፀጋዬ በበኩላቸዉ ድጋፉ ክልሎች ድረስ በመዉረድና የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ዩኒቨርሲቲዉ የሚሰጣቸዉን ፕሮግራሞች ለመከለስ እንደሚያግዝ ገልፀው ምስጋና ማቅረባቸውን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡