ጠ/ሚ ዐቢይ ለሮሃ ሕክምና ማዕከል ሜጋ ፕሮጀከት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

ሚያዚያ 02/ 2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለሚገነባው የሮሃ ሕክምና ማዕከል ሜጋ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ግንባታው በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለውን የሕከምና ማዕከል ሮሃ ግሩፕ የተሰኘና በጤና ዘርፍ የሚሰራ የአሜሪካ ኩባንያ በራሱ ወጪ የሚያስገነባው ነው።

የሕክምና ማዕከሉ በውስጡ አምስት ሆስፒታሎች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

በግንባታው በየአንድ ዓመቱ አንድ ሆስፒታል አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ መታቀዱም ነው የተነገረው።

ሮሃ የሕክምና ማዕከል በውስጡ የነርቭና የጀርባ፣ የህጻናትና እናቶችና የልብ ሕክምና ሆስፒታሎች፣ የሕክምና ትምህርት ቤት እንዲሁም የጥናትና ፈጠራ እና የማገገሚያ ማዕከላት እንደሚኖሩት ኢዜአ ዘግቧል።

ማዕከሉ 4 ሺህ 200 የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ለ7 ሺህ 200 ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራልም ተብሏል።